ቤተክርስቲያናችን

የቤተ ክርስቲያኗ አመሠራረት

ከተመሠረተ ሃያኛ ዓመቱን እያከበረ በሚገኘው በሙኒከ የኢትዮጵያውያን  የባህል ማዕከል አባላትና ከማዕከሉ ውጭ የሃይማኖት ፍቅር ባላቸው ጥቂት አባላት »አምልኮታችን» የምንገልጥበት  የራሳችን የሆነ ቤተ ክርስቲያን  ለምን አይኖረንም በማለት እንደ ዋዛ በተነሣው አሳብ ላይ ብዙ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ውይይቱ »አዎ» ያስፈልገናል በሚል አወንታዊ ስምምነት ተደመደመ

   ለዚህም ስምምነት ጉልህ ሚና ከተጫዎቱት ጠቃሚ ነጥቦች መካከል በስደት የሚወለዱ ሕፃናት በወቅቱ ና ባካባቢው ጥምቀተ ክርስትና እንዲያገኙ።-ከአገር ቤት ተወልደው የሚመጡ  ልጆችም ሃይማኖታቸውን፤ የሀገራቸውን ታሪክና ባህል እንዲማሩ፣እንዲያውቁ ለማድረግ።በአገራችን ሰላም ሰፍኖ በግዚአብሔር ቸርነት ወደ አገራችን እስክንመለስ ድርስ የምንኖረው በባዕድ ሃገርእንደ መሆኑ መጠን ሕፃናትና ጎልማሳ ልጆቻችን በሌላ ባህልና ወግ እየተዋጡ የራሳቸውን ሃይማኖት፣ባህልና ወግ ቀስ በቀስ እንዳይረሱ፤ የጥቅሙንና የጉዳቱንም መጠን በራሳቸው አእምሮ አመዛዝነው ለመረዳት እንዲችሉ ጠቀሜታውን ለልጆች በማስተማር አሳቡን ለማስጨበጥ   ነው። ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ነጥቦች እንዳሉ ሆነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በእምነት የወለደቻቸው ልጆቿን በየደረሱበት መጠበቅና ማፅናናት የተልእኮዋ አንዱና ዋንኛው ክፍል ነው ።

ይህም ማለት እስከ አጽናፈ ዓለም ተጉዞ ያላመኑትን የማሳመን፣ ያልተጠመቁትን የማጥመቅ ሥራ ማከናወን ያጠቃልላል ፡፡

  -ከአገራቸው ተሰደው በውጭ ሀገር  የመንፈሳዊ ሕይወት ራሃብተኞች ሆነው የሚኖሩ ወላጆች፡- አባቶቸና  እናቶች፤ አዛውንቶችና ሌሎችም ወገኖች ይህ የስደት ዘመን እስኪያልፍ ድረስ በቤተክርስቲያን እጦት ምክንያት በሃየማኖት ወደ ማይመስሉን ባዕዳን ቤት እንዳያቀኑ ማለትም  እንዳይሄዱ ፤ ይልቁንም የሃይማኖታቸውን እንድምታ፣የቀኖናቸውን ስልትና ትውፌት ጠብቀው እንዲቆዩ  ለማበረታታት

-አዲሱ ትውልድ በቤተ ክርስቲያን በሚያገኝው ትምህርት የራሱ የሆነ ኢትዮጵያዊ ማንነት ያለው

መሆኑን እየተገነዘበ በራሱ ሃይማኖትና በኢትዮጵያዊ ማንነቱ አንገቱን ቀና አድርጎ እንዲሄድ እንጂ ዛሬ ባገራችን ላይ በደረሰው ሰው ሠራሽ ሥቃይና መከራ፤ረሃበና ስደት  አንገቱን እንዳይደፋ፤በማንነቱ እንዲኮራ እንጂ እንዳያፍር፤ በሚደርስበት ቦታ ሁሉ  ፣እየተሸማቀቀ የበታችነት ስሜት እንዳይሰማው የሞራል ትምህርት በተቻለ አቅም እንዲያገኝ እድሉን ለመፍጠር  ነው።

  ከላይ እንደተዘረዘረው ለባህላችንና ለወጋችን እንግዳ በሆነ የምዕራብያውያን አስተምህሮና አመለካከት፤ እምነትና ባህል ሰለባ እንዳንሆን  በማሰብ በኢትዮጵያ የባህል ማዕከል ስም የተሰባሰቡ ጥቂት የቤተክርስቲያን ልጆች የ መሩት »ምን እናድርግ» ውይይት አድጎ የጥቂቶች ስብስብ ከመሆን አልፎ በየአንዳንዱ የቤተክርስቲያን ልጅ ልብ ውስጥ ሥር ሰድዶ ለመብቀል በመቻሉ »በእግዚአብሔር ስም ሁሉን  ማድረግ ይቻላል» በሚል ጠንካራ እምነት በመነቃቃት ጥቂቶቹን አሰልፎ፣ ብዙዎችን እያስተባበረ እነሆ  ከዚህ ሠፊና ታላቅ ለሀገርና ለወገን ኩራት የሆነ ቅርስ ባለቤት ለመሆን በቅቷል ።

ይህ መንፈሳዊ ተጋድሎ የተጀመረው በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ስም በተሰየመች ቤተክርስቲያን ጥላ ሥር በመሰባሰብ ነበር ።

/ የቤተ ክርስቲያኑ ስያሜ

የቤተ ክርስቲያናችንን አመሠራረት ስያሜና ታሪክ ስናነሳ ከአመሠራረቱ ታሪክ  ጎን ለጎን ምንጊዜም  የማይረሳ አንድ ታላቅ ጉዳይ አለ ።

  ይህም  ከእኛም አልፎ  አሁን ላለንበትና ለደረስንበት የዓለም ሁኔታ በአስተማሪነቱ፤ በመቻቻሉ፤በመከባበሩ፤ አብሮ በመኖርነቱ ፤ሁኔታ (tolerance) ታላቅ አንድምታ ያለውናእኛ ራሳችን ኢትዮጵያውያንም  የአባቶቻችን የነበረችውን ሀገራችን ኢትዮጵያን እንደገና ወደኋላ ተመልሰን እንድናይ ታላቅ የታሪክ በር የከፈተ ክሥተት ነበር ። 

የባህል ማዕከላችን አቋም የዘር፣የጎሣና የሃይማኖት ልዩነት የሌለበት  አገር ወዳድና ወገን አክባሪ በሆኑ ንጹሐን ኢትዮጵያውያን  የተቋቋመ እና ሁሉንም ያገራችን ዜጎች ያቀፈ ማኅበር በመሆኑ ከመሥራች የአመራር አባላት መካከል አንዱ የሆነው ወንድማችን  የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ  ቢሆንም  ለቤተ ክርስቲያናችን  ምሥረታ ያደረግነውን ስብሰባ በመደገፍ ከእኛ ጋራ አብሮ ተሰብሳቢ  ስለነበር በቤተ ክርስቲያናችን ስያሜ ላይ እያንዳንዱ ተሰብሳቢ የግል አሳቡን ሲሰነዝር ይህው ወንድማችን ኢትዮጵያዊ መብቱን ተጥቅሞ የቤተ ክርስቲያኑ ስያሜ ˝በቅድስት ማርያም ስም ˝ ቢሆን ደስ ይለኛል በማለት ያቀረበውን ስያሜ ሁሉም ተሰብሳቢ በታላቅ አክብሮት ስለተቀበለው እንሆ የቤተ ክርስቲያናችን መጠሪያ  »በእመቤታችን በቅድስት ማርያም ስም »ሆነ ።

ይኸው ወንድማችን ስያሜውን ብቻ ስጥቶን ከቤተ ክርስቲያን በር ዘወር አላለም ።  ይልቁንም እንደ ማንኛውም ክርስቲያን ለቤተ ክርሰቲያኑ ምሥረታ አስፈላጊውን ንዋየ ቅድሳት ለማሟላት በሚደረገው የገንዝብ አስተዋጽዖ ሁሉ የበኩሉን ያበረከተ  በመንፈሳዊ አገልግሎት መርሀ ግብር መሠረት ለትምህርትና ለቅዳሴ አገልግሎት ከሩቅ ቦታ ለሚመጡ ዲያቆናትና ካህናት እንደ ማነኛውም አባል ተራ ገብቶ የትራንስ ፖርት አገልግሎት በመስጠት  ከፍተኛ እገዛ ከማበርከቱም በተጨማሪ ቤተ ክርስቲያናችን አሁን ለደረሰችበት ዕድገት ካበቋት  አንዱ መሆኑን ስንገልጥ በከፍተኛ መንፈሳዊ ኩራትና ክብር ነው ።

ወንድማችን አሁንም ቢሆን የእመቤታችን ዓመታዊ በዓለ ንግሥ በሚከበርበት ዕለት እየተገኘ የክብረ በዓሉ ተካፋይ በመሆን እንደ ማናቸውም ጊዜ የተለመደ ድጋፉን ከማድረግ አልተቆጠበም ። በመሆኑም ለዚህ ኢትዮጵያዊ ታላቅ ሰው የምንለው ቢኖር ወንድማዊ ፍቅራችንና አክብሮታችን እንደተጠበቀ ሆኖ  የጌታችን፣ የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክረሰቶስ ምሕረትና ቸርነት፤የእናቱ የቅድስት ድንግል ማርያም  አማላጅነት፣በረከትና ረድኤት  ለሱና ለቤተ ሰቡ እንዲሆንለት የሁልጊዜ ጸሎታችን ነው ።

በሀገራችን በኢትዮጵያ በተፈጠረው ሰው ሠራሽ ችግር የምናዝን እኛ ኢትዮጵያውያን ከዚህ ብዙ ነገር መማር ይጠበቅብናል ። አባቶቻችን በብዙ ተጋድሎ ከውጭ ወራሪና ከፋፋይ ጠላት ጠብቀው ያስረከቡን ሀገራችንን  የመከባበርና የአብሮነት ጠብቀን ለማቆየትእንድንችልና ባልወረስንው የዘር በሽታና  የሃይማኖት አታካራ ተለከፍን አንተ የዚያ ፤ እኔ የዚያ ከመባባል አባዜ ወጥተን በፍቅር እጅ ለጅ ተያይዘን ይህን የመከራ ዘመን ዐቀበት ለማለፍ  እንድንችል አምላካችን  በቸርነቱ ይርዳን ።

ይህም ሁሉ ከስተት እኛ ኢትዮጵያውያን የዘር፣የጐሣና የሃይማኖት ልዩነት የማናውቅ ታላቅና ኩሩ ሕዝብ መሆናችንን ያየንበት የአባቶቻችን አብሮነት ታሪክ ታላቅ ነጸብራቅ ሲሆን ይህንንም ታሪካችን የሚያጎላ በነገረ ማርያም ላይ እንደሚከተለው ተጽፎ እናገኛለን።

»ድንግልም ከግንቦት ሐያ አንድ ቀን  ጀምራ እስከ ሐያ አምስት ቀን ድረስ ሳታቋርጥ በነዚህ ባምስቱ  ዕለታት ከመላእክት፣ከጻድቃንና ከሰማዕታት ጋር ትገለጥላቸው ነበር ። ክርስቲያንም፣እስላምም በገኀድ ተገልጻላችው ያዩዋት ነበር። በዓሏንም በፍጹም ክብር፣ በፍጹም ደስታ ያከብሩ ነበር» ። የሚል ነው ።(መቅድመ ተአምር ቍጥር ፳፭)።

/ የቤተ ክርስቲያኑ ከተመሠረተጀምሮ አገልግሎት የሚሰጥበት ቦታ

ዓመታዊ በዓለ ንግሥ ስናከብር ካልሆነ በስተቀር ሁልጊዜ እስካሁን ለመንፈሳዊ አገልግሎት የምንጠቀምበት

በBergmanstrasse 46 München »  በሚገኝው በ „Evangelisches Migrationszentrum“ በሚባለው ማዕከል አዳራሽ ውስጥ ሲሆን ከመንፈሳዊው  አገልግሎት ጎን ለጎን ሕፃናት ያገራቸውን ቋንቋ እንዲያውቁ ዘወትር እሑድ እሑድ የማስተማር ልምድ ባላቸው መምህራን በጎ ፈቃደኝነት በነፃ ትምህርት ይሰጣል ።

እንዲሁም የቅዳሴ ተሰጥዎ ለወጣቶችና ለአዛውንቶች በዲያቆን አዛርያስ አበበው አማካይነት በመሰጠት ላይ ይገኛል።

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ደም ከተመሠረተችበት ጊዜ  ጀምሮ ፈተና ያልተለያት ቢሆንም በእውነትና በዓለት ላይ ስለ ተመሠረተች ፈተናው አሸንፋት አያውቅም ።

»በእኔም ሰላምን እንድታገኙ ይህን ነገርኋችሁ። በዓለም ግን መከራን ትቀበላላችሁ፤ ነገር ግን ጽኑ እኔ ዓለምን ድል ነሥቸዋለሁና»።  የሚል ኪዳን ከአምላኳ ዘንድ አላትና ። ዮሐ፲፮፥፴፫ ።

ክርስትና ያለፈተና የለምና በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚነሣውን ፈተና ሁሉ እንደ ቃሉ በእግዚአብሔር ቸርነት፣በእናታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ተራዳኢነት እያለፍን ከዚህ ደርሰናል ። በእምነት ጸንተን

ከዚህም ለመድረስ የበቃነው ከምዕመናኑ ጥንካሬ ጋር የአባቶችን የካህናት አብሮነት ስላልተለየን በመሆኑ ምስጋናችን ልባዊ ነው ።

/ የታቦቱ መግባትና የቤተ ክርስቲያናችን የማዕረግ ስም

በነዚህ ሁሉ ዓመታት አያሌ ፈተናዎችና እንቅፋቶች ያጋጠሙን ቢሆንም፤ይህን ከመዘርዘር ይልቅ ፈተናዎቹን ሁሉ በልዑል እግዚአብሄር ፈቃድ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተራዳይነት  አልፈን አሁን የደረስንበትን ደረጃ ብንዘክር የተሻለ ሆኖ አግኝተነዋል።

ለዚህም በታላቅነቱ ከምናነሳውና ከምንኮራበት ክንዋኔ መሀከል አንዱ ለረጅም ጊዜ »ታቦት» እንዲገባልን በተደጋጋሚ የተማፅኖ ጥሪ ብናቀርብም ምንም አይነት ምላሽ አጥተንና ግራ ተጋብተን በነበረበት ወቅት አሳቡ የኛ ቢሆንም በዚህ ቦታ መመለክና መመስገን ግን የራሱ የእግዚአብሔር ቅዱስ  ፈቃድ ሆኖ ኑሮ እንደ ተአምር በሚቆጠር ሁኔታ ብፁዕ አባታችን አቡነ መቃርዮስ የኵቪክ ካናዳ፣ የአውስትራሊያና የቅድት ሀገር ኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም የአውሮፓ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ባላሰብነውና ባልጠበቅነው ሰዓት ሚያዝያ ፬ ቀን ፪ሺህ፮ ዓ/ም (13 April 2014) ባከበርነው ዓመታዊ በዓላችን ላይ ተገኝተው ለረጅም ጊዜ ስንመኝውና ስንጠብቀው የነበረውን ታቦት የማስገባት ሕልም ከመላው  ጀርመን እንዲሁም ከሲዘርላንድ የመጡ ብዙ ምዕመናንና

ካህናት በተገኙበት በዕለተ ሆሣዕና »ታቦተ ማርያምን» ባርከው በማስገባት ሕልማችንን አማናዊ አደረጉልን ።

ታቦተ ሕጉን ባርከው ከማስገባታቸውም በተጨማሪ በእኛ አእምሮ ውስጥ ያልነበረ ሌላ ተጨማሪ በረከት አደሉን ይኸውም ታቦቱ ከገባበት ዕለት  ጀምሮ ቤተ ክርስቲያኑ

»መንበረ ብርሃን »

 የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ »መልአከ ብርሃን» ተብሎ እንዲጠራ አዲስ ስያሜ በመስጠት በበዙ ሁኔታተጎድቶ የነበረውን  ሕይወታችን አክመውታል ።ለብፁዕ አባታችን አቡነ መቃርዮስ ረጅም ዕድሜ ከሙሉ ጤንነት ጋር የቤተ ክርስቲያን አምላክ እንዲሰጥል የዘወትር ጽሎታችንና ምኞታችን ነው ።

  ብፁዕ አባታችን አቡነ መቃርዮስ የሚሰጡት መንፈሳዊ አገልግሎት በኛ ብቻ አልተገደበም ።ይልቁንም በሌላው  የጀርመንና የአውሮጳ  ከፍል በመዘዋወር ምዕመናንን በማበረታታትና በማፅናናት፤ በአንዳንድ አካባቢ የነበረውን የቤተ ክርስቲያን የውስጥ ችግር በመፍታት አባታዊ ድርሻቸውን በስፋት ተወጥተዋል ።

ብፁዕ አባታችን አቡነ መቃርዮስ  በአሻፈንቡርግ ከተማ የሚኖሩ ምዕመናን በዚሁ ከተማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ስለሌለ እንዲከፈትላቸው ባቀረቡላቸው ጥያቄ መሠረት

»በኪዳነ ምሕረት» ስም አዲስ ቤተከርስቲያን ከፍተው፤ባርከውና አቋቁመው ሰጥተዋቸዋል ።

ብፁዕ አባታችን አቡነ መቃርዮስ ከየአብያተ ክርስቲያናቱ በሚደረግላቸው ጥሪ መሠረት በተደጋጋሚ እየተገኙ በተለያዩ የአውሮፓ ሀገሮች በመገኘት ብዙ መንፈሳዊ አገልግሎት አከናውነዋል ።

ብፁዕነታቸው የ መሩትን የአብያተ ክርስቲያናት መንፈሳዊ አገልግሎት ከመስጠት በተጨማሪ በምዕመናን ልጆቻቸው ቤት እየተገኙ  በስደት የደከመ አእምሮአቸውን በማበረታታት፤ የነገ ተተኪ ሕፃናት ልጆጃቸውም የወላጆቻቸውን ሃይማኖትና ታሪክ፣ባህልና ወግ እየተማሩ ጠብቀው እንዲያድጉ ያላሠለሰ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው አባታዊ ምክራቸውን በሰፊው ለግሰዋል ። 

ከዚሁ በተጨማሪ ቤተ ክርስቲያናችን ሕፃናትና ወጣቶች በሀገራቸው ሁለንተናዊ ዘርፍ ተኮትክተው እንዲያድጉ ፤ የማንነታቸው መገለጫ በሆነው በሀገራቸው ቋንቋ የንባብና የጽሁፍ ትምህርት እንዲከታተሉ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች ።

/ የቤተ ክርስቲያናችን የወደፊት ዕቅድ

ቤተ ክርስቲያናችን ያበረከተችወና እያበረከተች ያለው አስተዋፅኦ ቀላል ነው ባይባልም ፤ ከዚህ በበለጠ ገና ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል ። ይህን መንፈሳዊ አገልግሎት በቀጣይነት ለማካሔድ እያንዳንዱ ምዕመን፤ ካህን፤ዲያቆን ሁሉ የየራሱን አስተዋፅዖ  ማድረግ ይጠበቅበታል ። ምክንያቱም እስካሁን የዘረዘርናቸው ውጥን አገልግሎቶች ሳይቋረጡ እንዲቀጥሉ የምናስኬድበት ቋሚ ቤተክርስቲያን

ስሌለለን ቤተክርስቲያን ለማግኘት ብዙ ሙከራ ቢደረግም እስካሁን አልተሳካም ። ይሁን እንጂ ክርስቲያን ተስፋ አይቆርጥምና ተስፋ ሰጪ የሆኑ ምልክቶች በመኖራቸው ጥረታችንን አጠናክረን መቀጠል ይጠበቅብናል ።ያቀድነውም እንደሚሳካልን እምነታችን በእግዚአብሔር ጽኑእ ነው ።

ብፁዕ አባታችን አቡነ መቃርዮስ የኩቤክ ካናዳ፣ አውስትራሊያና የቅድት ሀገር ኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም የአውሮፓ ረዳት ሊቀ ጳጳስ አብያተ ክርስቲያናትን ለማጠናከር ሲመቻቸው በአካል እየተገኙ፣በሥራ ብዛት፣በሀገር ርቀት አልመቻቸው ሲል ደግሞ በሐሳብ፣በጸሎት፣ከበፁዕነታቸው  የምንፈልገውን ማነኛውን ሁኔታ በፍጥነት በመላክ አብረውን  ከመሆናችውም በላይ

መልአከ ፀሐይ ቀሲስ አበባው አዳነ በሲዊዘርላንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሀገረ ስብከት ሊቀ ካህናት፤ የበርን ደብር ፀሐይ አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪን የቤተክርስትያናችን የበላይ ጠባቂ 

መልአከ ሰላም ቀሲስ መሠረት አለነ  የቤተክርስትያናችን አስተዳራሪ  ሆነው እንዲያገለግሉ በብፁዕ አባታችን ተሹመዋል በተጨማሪም በተወዳጁና ታታሪው ወንድማችን  ዲያቆን አዛርያስ አበባው  እና ለሌሎችም ልጆች ትልቅ አርአያ በሚሆነውበምንወደው ልጃችንና ወንድማችን  ዲያቆን ዳንኤል ክበበው  እንዲሁም  ለግብረ ዲቁና ራሳቸውን እያዘጋጁ ባሉ ብዙ አንባብያንና አናጉንስጢሳን አማካይነት መንፈሳዊ አገልግሎቱ  ተጠናክሮ ቀጥሏል ።